ኢትዮጵያ ከጆርዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ጽኑ ፍላጎት አላት

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከጆርዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በጆርዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

ተቀማጭነታቸውን አቡዳቢ በማድረግ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ጆርዳን እና ሶሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማጂድ ታሊጅ አል ኳታርኔህ ዛሬ አስገብተዋል።


 

አምባሳደር ዑመር በስራ ቆይታቸው የኢትዮጵያ እና የጆርዳንን የሁለትዮሽ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው ጠቅሰው በዚህ ረገድም የጆርዳን ባለሀብቶች በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝም እና አገልግሎት ዘርፍ መሰማራት የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች እንዳሉ አመልክተዋል።

በተጨማሪም አምባሳደር ዑመር ለዋና ፀሐፊው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ዘርፍ ሪፎርሞች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

የጆርዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማጂድ ታሊጅ አል ኳታርኔህ የኢትዮጵያ መንግስትን የሪፎርም ስራዎችን አድንቀዋል።

ጆርዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸው በወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳዮች እና ጆርዳን ስለሚኖራት ገንቢ ሚናም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጆርዳን መንግስት አምባሳደሩ በስራቸው ለሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውንም በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም