ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ቻይናን የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር የሚያጠናክር ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኮንፍረንሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ ኤስያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ንጉሥ ከበደ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ፣ የጃንግዙ ግዛት የንግድ መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ሲ ዮንግና የግዛቲቱ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

አምባሳደር ንጉሥ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያና ቻይና የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።

ይህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን እያደረገች ያለው ጉዞ እውን እንዲሆን የሚያግዝ ነው ብለዋል።


 

የቻይናዋ ጃንግዙ ግዛት በዚህ የትብብር ሂደት አይተኬ ሚና እንዳላት ገልፀዋል።

የግዛቲቱ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ የኢኮኖሚና የንግድ ትብብርን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።

የኢትዮ-ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት በኢኮኖሚና ንግድ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የቻይና ጃንግዙ ግዛት የንግድ መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ሲ ዮንግ ኢትዮጵያ ለግዛቲቱ ባለሃብቶች ምቹ የኢኮኖሚና የንግድ መዳረሻ እንደሆነች ተናግረዋል።

በተለይ የግዛቲቷ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም