ቀጥታ፡

ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተሰጡ የጤና አገልግሎቶች የእናቶች የሞት ምጣኔ ቀንሷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ትብብር በሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነስ ማስቻሉ ተገለጸ።

የኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ የእናቶችና ሕጻናት ልዩ ህክምና ማዕከል በአዲስ አበባ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ እንዳሉት መንግስት በቅድመ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ ቀርጾ እየተገበረ ነው ብለዋል።

መንግስት፣ የግል ዘርፉና አጋር ድርጅቶች ባለፉት ዓመታት ባደረጉት ርብርብ በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ እመርታ መመዝገቡንም አንስተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት የአጋር ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ትብብር በሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር መቀነስ ተችሏል ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በ2030 የእናቶችና ህጻናት ሞት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ ለያዘችው ግብ እውን መሆን ከመንግስት ባለፈ የግል ዘርፉና አጋር ድርጅቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስረድተዋል።

ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት በራስ አቅምና ሃብት በማሰባሰብ ዘላቂ የጤና አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ 60 በመቶ ያህል ወጪውን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።


 

የኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አበበ ሽብሩ (ዶ/ር) እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ዓመታት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ትርጉም ያለው ውጤት መጥቷል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ መንግስት ለአጋር ድርጅቶች ምቹ ፖሊሲዎች ማውጣቱን እንደ ምቹ ሁኔታ አንስተዋል።

ድርጅቱ በአገሪቷ በሁሉም አካባቢዎች የወሊድና የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ ከተያዘው ወር ጀምሮ በ23 ጤና ጣቢያዎች ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነጻ የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ነው ያብራሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም