በግማሽ ዓመቱ ከ209 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሕገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ተወግደዋል- ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በግማሽ ዓመቱ ከ209 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሕገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ተወግደዋል- ባለስልጣኑ
አዳማ፤ የካቲት 18/2017 (ኢዜአ)፦ በግማሽ ዓመቱ ግምታቸው ከ209 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ሕገ ወጥ የምግብና የመድኃኒት ምርቶች ማስወገዱን የኢትዮጵያ መድኃኒት እና ምግብ ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ የምግብና የጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ዘርፍን የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።
በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳደርን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ የምግብና የመድሀኒት ዝውውሮች የህብረተሰቡን ጤና በቀጥታ ለጉዳት ከመዳረጋቸው ባሻገር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚዳርጉ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በዚህም ሕገ ወጥ የመድሀኒትና የምግብ ምርቶችን በቅንጅት መከላከል አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
በባለስልጣኑ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፋይዛ ቢያ በበኩላቸው በሕገ ወጥ የመድሀኒት እና የምግብ ምርቶችን ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በገበያ ቅኝቶች፣ በኢንስፔክሽን፣ በህብረተሰብ ጥቆማ ከ177 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ለሰው ልጅ ምግብነት የማይውሉና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ምርቶች ሲወገዱ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምግብ ምርቶች ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ መደረጉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል 32 ሚሊዮን 756 ሺህ ብር የሚያወጣ የመድኃኒት ምርት ሲወገድ፤ 277 ሺህ ብር የሚገመት መድኃኒት ደግሞ ተሰብስቧል ብለዋል።