ቀጥታ፡

የቻይና ጃንግዙ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ጃንግዙ ግዛት ባለሀብቶች ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በጃንግዙ ግዛት የንግድ ቢሮ ዳይሬክተር ጄነራል ሲ ዮንግ ከተመራ የቢዝነስ ልዑክ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም የፈጠረውን ምቹ ከባቢ በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የጆንግዙ ግዛት ንግድ ቢሮ ዳይሬክተር ጄነራል ሲ ዮንግ ኢትዮጵያ እና ቻይና ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የግዛቷ ባለሀብቶች በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው እና ቢሮው ይህንኑ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ስምምነት ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከሶስት ሺህ በላይ የቻይና ድርጅቶች በኢንቨስትመንት ተሰማርተው እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም