ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በመሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በመሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለጎሮቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ በጋራ መልማት፣ ማደግና መበልጸግን ጨምሮ የጋራ ደህንነትን በትብብር ማስጠበቅን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ለጎሮቤት ሀገራት ሰላምና እድገት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር አብሮ የመልማትና የማደግ መርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫም እንዳለው ይታወቃል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና ለመከላከል እየወሰደች ያለው ቁርጠኝነት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አስራት(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ አምራች ዜጋ ያለበት፣ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ እንዲሁም ስብጥር ያለው ማህበረሰብ የሚኖርበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን ጠቁመው፤ ቀጣናውን በመንገድና በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ለማስተሳሰር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለአብነት አንስተዋል።

የቀጣናው ሀገራት እንደ ድርቅና ሽብርተኝነት ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጎልበት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም