ቀጥታ፡

ሴቶች በዓድዋ ጦርነት ያሳዩት ጥበብና ብልሃት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ሊደገም ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፡- ሴቶች በዓድዋ ጦርነት ያሳዩት ጥበብና ብልሃት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ሊደገም እንደሚገባ ተገልጿል።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ለመታደግና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተደረገው የዓድዋ የተጋድሎ ታሪክ ሴቶች የጎላ ሚና ነበራቸው።

በጦርነቱ በቀጥታ በመሳተፍ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ አርበኞችን በማጀገን ለድሉ መገኘት ያሳዩት ብልሃትና ጥበብም በታሪክ ሲዘከር ይኖራል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች እንደገለጹት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት ሆና በአለም እንድትጠቀስ ዋነኛ ምክንያት ነው።

ጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ህልውናቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ዘር ያለ ልዩነት ለአንድ ዓላማ በጋራ ቆመው ድል የተቀዳጁበት ነው።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺአምላክ ገብረማርያም እንዳሉት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያስመዘገበቻቸው ያሉ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የዘመኑ ሴቶች ሊተጉበት የሚገባ የአርበኝነት ጀብዱ ነው።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሴቶች ተሳትፏቸውን ማጉላት ይገባቸዋል።

መምህርት አቶሚ አበበ(ዶ/ር) በበኩላቸው ለአንድ ሀገር አለም አቀፍ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ጉልዕ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።

በምግብ ራሷን የቻለችና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የተላቀቀች ሀገር በሌሎች ሀገራት አሉታዊ ተጽዕኖ ስር እንደማትወድቅም አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የከፈሉት መስዕዋትነት ለሌሎች ሀገራት መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ዘመን ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንደ ሀገር መቆሟ ለሌሎች ምሳሌ መሆኗን ጠቅሰው፣ የኢኮኖሚ አቅምን በማጠናከር የአሸናፊነት ታሪክን መድገም ይገባል ብለዋል።

ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሴቶች ሚናቸውን ማጉላት እንዳለባቸው በመግለጽ።

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ምክር ቤት አባል ነስራ ዑዳ እንዳሉት ሴቶች የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት በከፈለው መስዋዕትነት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሰላምና ልማት አርበኛ እንደመሆኑ ሴቶች ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሚናቸውን የበለጠ ማጉላት አለባቸው ነው ያሉት።

ሴቶች በዓድዋ ጦርነት ያሳዩት ጥበብና ብልሃት አሁን ላይ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሊደግሙት እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ያነሱት።

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የልማት ስራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑና በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት እንዲያድግ ሴቶች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

ሴቶች ቤተሰብ ከማስተዳደር ጀምሮ በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን አቅም የበለጠ በመጠቀም የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም