የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ምስረታና ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ምስረታና ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 18/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ምስረታና ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
በመርኃ ግብሩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) ጨምሮ ነጋዴ ሴቶች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶች ነጋዴዎችንና የንግድ ባለሙያዎችን ለማብቃት እና ለመደገፍ የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል።
ማህበሩ ሴቶች በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና በመገንዘብ ለሴቶች ጥቅም የሚሟገትና የንግድ እድሎችን የሚያሻሽል ጠንካራ መድረክ ለመፍጠር የሚሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም የአቅም ግንባታ እና የፋይናንስ አጠቃቀምን በማሻሻል ለሴቶች የተመቸ ሁለንተናዊና የበለጸገ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ነው ተብሏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የሴት ነጋዴዎችን ጥቅም በተደራጀ መንገድ የሚያስከብር መሆኑን ገልጸዋል።
አደረጃጀቱ የንግድ ስርአቱን አካታችነት፣ ጤናማነት እና ተደራሽነት ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ እና ጠንካራ ሴቶች የሚፈሩበት አደረጃጀት መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም በንግድ ሂደት ውስጥ በሴት ነጋዴዎች ላይ የሚያጋጥሙ ስርአታዊ እና መዋቅራዊ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ በጋራ የሚሰራበት መሆኑን አመላክተዋል።
ይህንን አደረጃጀት ማጠናከር እና ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ ማህበሩ ሴቶችን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በመድረኩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እና የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።