ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የያዘቻቸውን ግቦች እውን ለማድረግ አበክራ እየሰራች ነው - አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የያዘቻቸውን ግቦች እውን ለማድረግ አበክራ እየሰራች ነው - አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የያዘቻቸውን ግቦች እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና በተመድ የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ-ግብር(ዩኤን ሀቢታት) የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገለጹ።
አምባሳደር ደመቀ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ጋር በመሆን ተቀማጭነታቸውን በናይሮቢ ላደረጉ ሚሲዮኖች ኢትዮጵያ ለሁለተኛው የተመድ የምግብ ስርዓት ጉባዔ እያደረገች ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት ጉባዔውን ለማሰናዳት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የያዘቻቸውን ግቦች ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተገበራቸው ስላሉ መርሃ ግብሮችም ገለጻ አድርገዋል።
መስኖን ማዕከል ያደረገ ግብርና፣ ለአየር ንብረት የማይበገር ግብርናን ማስፋት፣ የግብርና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ፣ የተሻሻለውን የምርጥ ዘር አዋጅ፣ የግብርና ንግድ ክላስተሮች እና የኤክስቴንሽን አገልግሎቶች ከኢኒሼቲቩ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የሌማት ትሩፋት እና አረንጓዴ አሻራ የምግብ እና የስርዓተ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጥር ወር 2016 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) ያገኙት የከበረ የአግሪኮላ ሜዳልያ ሽልማት ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ያገኘችውን ስኬት ምስክር መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትና የዓለም ዋነኛ አንገብጋቢ አጀንዳ ነው ያሉት አምባሳደሩ ጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለጉባዔው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ጉባዔውን ከጣልያን ጋር በትብብር ለማዘጋጀት ላሳየችው ፈቃደኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
ሁለተኛው የተመድ የምግብ ስርዓት ጉባዔ ሐምሌ 21 እና 22 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።