በአጿማቱ ወቅት የመደጋገፍና የመተጋገዝ እሴቶችን በማጠናከር የወገኖቻችን አለኝታ መሆን አለብን - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአጿማቱ ወቅት የመደጋገፍና የመተጋገዝ እሴቶችን በማጠናከር የወገኖቻችን አለኝታ መሆን አለብን - የኃይማኖት አባቶች

ባህርዳር፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፡- በአጿማቱ ወቅት የመደጋገፍና የመተጋገዝ እሴቶችን በማጠናከር የወገኖቻችን አለኝታ መሆንን በተግባር ማሳየት አለብን ሲሉ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የአቢይ ፆም የተጀመረ ሲሆን የታላቁ የረመዳን ፆም ደግሞ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚጀመር ይሆናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ከምእመናኑና አጠቃላይ ከህብረተሰቡ በተለይም ማህበራዊ እሴቶችን ከማጠናከር አንፃር ምን እንደሚጠበቅ የኃይማኖት አበቶችን አነጋግሯል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባህርዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን፤ በፆሙ በተለይም በችግርና በህመም ላይ የሚገኙትን በመጠየቅ በመተዛዘንና በመተጋገዝ መሆን አለበት ብለዋል።
ከምንም በላይ ፍቅርና ሰላምን በመስበክ ለይቅርታ ቦታ መስጠትና መልካምነትና ርህራሄን በተግባር ማሳየት ይገባል ነው ያሉት።
የመጠያየቅ፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ከፆሙ መሰረታዊ መገለጫዎች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሀመድ አንዋር፤ ታላቁን የረመዳን ወር ለመቀበል እየተዘጋጀን ያለነው ከጥፋት በመራቅ፣ ይቅርታን በማስቀደምና ደግነትን በመሰነቅ ነው ብለዋል።
በመሆኑም አጠቃላይ ህዝበ ሙስሊሙ በዚሁ እሳቤ በተግባር የሚታይ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የተጀገሩትን በመደገፍና የታመሙትን በመጠየቅ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በታላቁ የረመዳ ወር ቀኑን በፆም፤ ሌሊቱን በዱአ በፅናት ለማሳለፍ መዘጋጀት እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በረመዳን ወር መልካምነትና ሰብአዊነትን በማስቀደም አንድነትን፣ መፈቃቀርንና መተሳሰብን በመላበስ መሆን አንዳለበት ገልጸው ይህንን መልካም እድል ተቀብሎ ለመተግበር ሁሉም እንዲዘጋጅ መልእክት አስተላልፈዋል።