ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ለዘርፉ እድገት ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ይሰራል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ለዘርፉ እድገት ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ይሰራል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
ስንቅሌ፤ የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፦ ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ለዘርፉ እድገት ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አስታወቁ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኘው ስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ ማህበረሰብ አቀፍ ሎጅን መርቀው ለአገልግሎት አብቅተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ የሚገኘው ስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ በ1964 ዓ.ም የተመሠረተ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ የማህበረሰብ አቀፍ ሎጁን መርቀው ሲከፍቱ እንዳሉት ሚኒስቴሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት ባለድርሻ አካላትን በሳተፈ መልኩ የተቀናጀ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ለዘርፉ እድገት ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ የተገነባው ሎጅም የቱሪዝም ልማት የባለድርሻ አካላትን ብርቱ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የስንቅሌ የዱር እንስሳት መጠለያ በገዳ ስርዓት አማካኝነት ተጠብቆ ለዛሬ በመድረሱ የአካባቢው ማህበረሰብ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
ይህ ከገዳ ሥርዓት የመነጨው እንስሳትን የመንከባከብና የመጠበቅ እሴት በሌሎች አካባቢዎችም መስፋትና ለዘርፉ ማስተማሪያነት መዋል የሚገባው እሴት እንደሆነም አንስተዋል።
ስንቅሌ የቆርኬዎች መጠለያ ኃላፊ አቶ ገመቹ ለታ በበኩላቸው መጠለያው ውስጥ የነበሩ ቆርኬዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ እንደነበረ አስታውሰዋል።
በአባ ገዳዎች በተላለፈ ድንጋጌ የተጠናከረ ጥበቃ መደረግ ከተጀመረ ወዲህ ግን ቁጥራቸው ተባዝቶ በዚህ ወቅት 400 የሚገመቱ ቆርኬዎች በአካባቢው ማህብረሰብ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
የአካባቢው አባ ገዳ ራማቶ አባቡቦ እንዳሉት በአካባቢው በቆርኬዎች ላይ ተደቅኖ የነበረውን የመጥፋት አደጋ ለመግታት አባ ገዳዎች ቆርኬዎችን መጠበቅ የሚያስችል ውስኔ ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ።
ውሳኔው ቆርኬዎች እንደ አንድ የአካባቢው ጎሳ አባል እንዲታዩ እና በምንም መልኩ ቆርኬዎቹን የነካ ጎሳውን አባል እንደነካ እንዲቆጠር ተደንግጎ ቅጣት እንደሚጣል ተናግረዋል።
በውሳኔው መሰረትም የማህብረሰቡ ግንዛቤ እንዲቀየር በመደረጉ ሊጠፉ ተቃርበው የነበሩ ቆርኬዎች በአካባቢው ማህብረሰብ እየተጠበቁ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከመጠለያው ለእንስሳት መኖ የሚውል ሳር አጭደው እየተጠቀሙ ሲሆን ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብን የባለቤትነት መንፈስ ማነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤ የኢትዮጵያ ዱር አንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን መኮንን እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።