በአፍሪካ ሰላምን በማረጋገጥ የአህጉሪቷን ብልፅግና እውን ለማድረግ ወጣቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሰላምን በማረጋገጥ የአህጉሪቷን ብልፅግና እውን ለማድረግ ወጣቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካ ያላትን አቅም ተጠቅማ ብልፅግናዋን እንድታረጋግጥ ወጣቶች በሰላም ግንባታ ላይ አበክረው እንዲሰሩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥሪ አቀረቡ።
የአፍሪካ የወጣት መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ጉባዔ ከትናንት የካቲት 16 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
አቶ ኃይለማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት አፍሪካ ጥንታዊ ታሪክ፣ ብዝሃ ባህልና ዕምቅ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለች ናት፡፡
በዚህም በአህጉሪቱ ሰላምን በማስፈን በሀብቷ ልክ ሁለንተናዊ ልማቷን እንድታረጋግጥ በጋራ መስራት ይጠይቃል።
የአፍሪካ 60 በመቶ ሕዝብ ወጣት በመሆኑ የወጣቱን አቅም ለሰላም ግንባታና ለአህጉሪቷ ሁለንተናዊ ልማት መረጋገጥ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተሻለችና ብሩህ አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ወጣቶች አቅማቸውን አውጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ዕውቁ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙምባ አፍሪካ ትናንታችሁ፣ ዛሬያችሁ እንዲሁም የነገ መፃዒ ተስፋችሁ ናት በማለት ወጣቶቹ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የአጀንዳ 2063ን ጨምሮ የአፍሪካን ታላላቅ ግቦች ዕውን ማድረግ የሚቻለው በወጣቱ ትውልድ በመሆኑ ወጣቶች ለተሻለች አፍሪካ ግንባታ በአንድነትና በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰላም ውይይት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ጫላ አሰፋ አፍሪካ የፅናት ተምሳሌትና የበርካታ ሃብት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰዋል።
ወጣት አመራሮች አፍሪካን ለመለወጥ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝቧል።
ውይይቱ ወጣቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚወያዩበት እና ትብብር የሚፈጥሩበት መሆኑ ነው የተገለጸው ።