የተራቆተ መሬትን በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን ለማውረስ እየሰራን ነው-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተራቆተ መሬትን በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን ለማውረስ እየሰራን ነው-አርሶ አደሮች
መተማ፤ የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፡-በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተራቆተ መሬትን በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን ለማውረስ እየሰሩ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ በተያዘው የበጋ ወራት በሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እስካሁን ድረስ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት መልማቱን አስታውቋል።
በወረዳው የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አወቀ ስመኘው ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች በአካባቢያቸው ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል።
በዚህም የደረቁ ምንጮች መልሰው መጎልበታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ የተጎዱ መሬቶችም በማገገማቸው ለአርሶ አደሩ ዘላቂ ሀብትን ለማፍራት እያስቻሉት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ዘንድሮ እየተከናወነ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በንቃት በመሳተፍ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ አካባቢን ለማስረከብ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በየዓመቱ በሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተሳተፉ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላኛው አርሶ አደር አበራ አስሬ በበኩላቸው፣ ለልጆቻቸው የተራቆተ ሳይሆን የለማ አካባቢን ለማወረስ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"ነገን ዛሬ መስራት እንዳለብን ካለፉት ዓመታት ልምድ ወስደናል" ያሉት አርሶ አደሩ፣ የለሙ ተፋሰሶች የእንስሳት መኖ ለማግኘት ከማስቻል ባለፈ በንብ ማነብ ሥራ በመሰማራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ሥራ የማንንም ቀስቃሽነት ሳይጠብቁ ልማቱን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው፣ በዚህም ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታሁን ፍስሃ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው በነቃ የህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ፣ የልማት ሥራው በተጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአራት ወረዳዎችና ሦስት ከተማ አስተዳደሮች ከ400 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ ተከናውኗል።
በዘንድሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በ91 ተፋሰሶች ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬትን ለማልማት ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል።
በልማቱ የዞኑ ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ ሥራውም በዕቅዱ መሰረት በሃላፊነት ስሜት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።