ቀጥታ፡

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በጋምቤላ ክልል የስደተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴን ለመመልከት ጋምቤላ ገቡ

ጋምቤላ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፦ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞችን የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴ ለመመልከት ጋምቤላ ገብተዋል።

በዚህም የሰባት አገራት አምባሳደሮችና በዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ጀኒፈር ቢቶንድ ጋምቤላ የገቡ ሲሆን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዓለሚቱ ኡሞድ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው መክረዋል።


 

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ፤ ክልሉ በርካታ ስደተኞችን በማስጠለል አስፈላጊውን ጥበቃ የሰብዓዊ ድጋፍና የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ለስደተኞቹ በተለይም የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎችም አገልግሎቶች ተደራሽ በማድረግ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ለዚህም የክልሉ ብሎም የፌዴራሉ መንግስት በትጋትና በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ለስደተኞች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ የባለድርሻ አካላት ትብብር፣ እገዛና ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን፤ በክልሉ ያለው የስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አንስተው መንግስት በዚሁ ልክ የተቻለውን ሁሉ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ በተለይም አጋር አካላት ለሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት የበኩላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በጋምቤላ ከተገኙት አምባሳደሮች መካከል በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሿ ታባህ፤ በክልሉ ስደተኞችን ከመቀበል ጀምሮ እየተደረገ ላለው ድጋፍና ጥበቃ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ተግባር በመደገፍ በተለይም ለጋሽ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በውይይቱ የካናዳ፣ የጀርመን፣ የኦስትሪያ፣ የቤልጅዬም፣ የኖርዌይ፣ የፊንላንድ እና የሉክዘምበርግ ሀገራት አምባሳዳሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ በቀጣይ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም