ተፋሰስ ልማት ሕልውናውን የመለሰው ጨርጨር ሐይቅ

የጨርጨር ሐይቅ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሐብሮ፣ ኦዳ ቡልቱም እና ቦኬ ወረዳዎች አካሎ ይገኛል።

የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ተከትሎ ጨርጨር ሐይቅ ከደረቀ ከ11 ዓመታት በኋላ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ተመልሷል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ፍጹም አማረ ለኢዜአ እንደሚሉት ጨርጨር ሐይቅ ለ11 ዓመታት ደርቆ ቆይቷል።

ባለፉት አመታት የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ ስራዎች አካባቢ እንዲለመልምና የሐይቁ ሕልውና እንዲመለስ ማስቻሉን ይናገራሉ።

ጨርጨር እንደ ሐረማያ ሐይቅ የውኃ መጠኑ እየጨመረ መጥቷል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአካባቢው በተሰሩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ሐይቁ ዳግም ሕልውናው እየተመለሰ መምጣቱን ይናገራሉ።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሱሌይማን መሀመድ በበኩላቸው የሐይቁን ደህንነት ለማስጠበቅና እና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ለማጎልበት አስቻይ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአካባቢው ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በአሳ ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም።

ሐይቁ በሁለት ዓመታት ውስጥ መጠኑን ከነበረበት ከ200 ሄክታር በሶስት ዕጥፍ በማሳደግ ወደ 600 ሄክታር መሬት ማካለል ችሏል።

በክልሉ መንግስት ከተለዩ 12 የኢኮ ቱሪዝም ስፍራዎች አንዱ የጨርጨቅ ሐይቅ ነው።

በዚህም ሐይቁን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የጥናት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ሱሌይማን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም