ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ እየተገበረች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ እየተገበረች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ዛሬ በቻይና የአለማቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የተመራን ልዑክ ተቀብለን በሁለቱ ሃገራት የንግድ ግንኙነትና ፕሮሞሽን ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗንና ከቻይና ጋርም በቀጣይ ይህን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረን አስገንዝቤያለሁ ሲሉም ገልጸዋል።
የንግድ ግንኙነቱ ስለሚጠናከርበት ሁኔታም ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ልዑካን ቡድኑ በቆይታቸው ተዘዋውረው በተመለከቱት የለውጥ ውጤቶች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል ብለዋል።
ቻይና በቀጣይ ሐምሌ በምታዘጋጀው 3ኛው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ እንድንሳተፍ ግብዣ አቅርበውልናል ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረስብ የቻይናን ገበያ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ዝግጅት ተደርጎ እንደምንሳተፍ መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉም ገልጸዋል።