የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት ሲከሰት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በጥቂቱ - ኢዜአ አማርኛ
የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት ሲከሰት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በጥቂቱ
ከቤት ውጭ ከሆኑ፦
ከዛፎች፣ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና ሌሎች ወድቀው ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ እና ገላጣ ሜዳ አካባቢ መቆየት።
በቤት ውስጥ ከሆኑ፦
በበር መቃኖች፣ ኮርነሮች እና ኮሪደሮችን ተጠግቶ ማሳለፍ።
ከእሳት ምድጃዎች፣ ከተሰቀሉ ፍሬሞች እና የግድግዳ ጌጦች፣ ከመጽሐፍ መደርደሪያዎች እንዲሁም ከመስኮት አካባቢ መራቅ።
የጋዝ ምድጃዎችን በተቻለ ፍጥነት ማጥፋት ካልሆነም ከአካባቢው መራቅ።
በትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥ ከሆኑ፦
ከሕንጻዎቹ ለመውጣት አለመሞከር፣ አሳንሰር(ሊፍት) በፍፁም አለመጠቀም።
ከደረጃዎች አካባቢ መራቅ።
መኪና እያሽከረከሩ ከሆነ፦
የኤሌክትሪክ መተላለፊያ ምሰሶዎችን፣ ዛፎችና ሽቦዎች አካባቢ አለመቆም፣
የኤሌክትሪክ መስመር ምሰሶዎች እና ሽቦዎች ተሽከርካሪው ላይ ከወደቁ ከመኪናው ለመውጣት አለመሞከር፣
በተቻለ ፍጥነት ገላጣ ወደሆነ አካባቢ መኪናን ማቆም።
በያዝነው አመት በሀገራችን አዋሽ ፈንታሌ ላይ በተለያዩ ሬክተር ስኬል መጠን በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ መሆኑን፤ በዚህም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ሰፋ ያለ ጥናት እና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
በየጊዜውም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ንዝረት ሲከሰት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
ዛሬ የካቲት 16/2017 ከለሊቱ 8 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 3 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መከሰቱን የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።