ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ለውጥ ወጣቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦ በራሷ አቅም ሁለንተናዊ ልማቷን ያረጋገጠች አፍሪካ ዕውን ለማድረግ ወጣቶች በሰላም ግንባታ ላይ አበክረው እንዲሰሩ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ኃይለማርያም ይህን ያሉት በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረውን የአፍሪካ የወጣት መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

አቶ ኃይለማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት ጥንታዊ ታሪክ፣ ብዝሃ ባህልና

ዕምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ያላትን አፍሪካ ሰላምን በማስፈን በሀብቷ ልክ ሁለንተናዊ ልማቷን ታረጋግጥ ዘንድ በጋራ መስራት ይጠይቃል።


 

የአፍሪካ 60 በመቶ ሕዝቧ ወጣት መሆኑን ያወሱት አቶ ኃይለማርያም ይህን የወጣት አቅም ለሰላም ግንባታ መጠቀም ብሎም ለአህጉሪቷ ሁለንተናዊ ልማት መረጋገጥ ማዋል እንደሚገባ ተናገረዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የተሻለችና ብሩህ አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ወጣቶች አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ለአጀንዳ 2063 ስኬት ወጣቶች አይተኬ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ዕውቁ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙምባ አፍሪካ ትናንታችሁ፣ ዛሬያችሁ እንዲሁም የነገ መፃዒ ተስፋችሁ ናት ብለዋል።

የአጀንዳ 2063ን ጨምሮ የአፍሪካ ታላላቅ ግቦች ዕውን ማድረግ የሚቻለው በወጣቱ ትውልድ በመሆኑ ወጣቶች ለተሻለች አፍሪካ ግንባታ በአንድነትና በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰላም ውይይት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ጫላ አሰፋ አፍሪካ የፅናት ተምሳሌትና የበርካታ ሀብት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰዋል።

ወጣት አመራሮች አፍሪካን ለመለወጥ ሚናቸው መጠቀም እንዳለባቸውም አንስተዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖረው ውይይት ወጣቶች የሚገጥሙንን ችግሮች ለመፍታት የምንወያይበትና ትብብር የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም