ቀጥታ፡

የወለጋ ሕዝብ በታጠቁ ሃይሎች ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ወደ ልማት እንቅስቃሴ ገብቷል- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2017(ኢዜአ)፦የወለጋ ሕዝብና አካባቢው ባለፉት ዓመታት የታጠቁ ኃይሎች ካደረሱት ጉዳት አገግሞ በቁጭትና በእልህ ወደ ተሟሟቀ የልማት እንቅስቃሴ መግባቱን እንደተገነዘቡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ከቃል እስከ ባህል፥ በወለጋ ስኬት ምልከታዬ የሚል ርዕስ ሰጥተው ባሰፈሩት ጽሁፍ በብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ከአራቱም ወለጋ ዞኖች ከተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የነቀምቴ ከተማና የምስራቅ ወለጋ የልማት ሥራዎችን የመጎብኘት ዕድል አግኝተናል ያሉት ሚኒስትሩ በውይይቱም ሆነ በጉብኝቱ የወለጋ ሕዝብና አካባቢው ባለፉት ዓመታት የታጠቁ ኃይሎች ካደረሱት ጉዳት  አገግሞ በቁጭት እና በእልህ ወደ ተሟሟቀ የልማት እንቅስቃሴ መግባቱን ተገንዝበናል ብለዋል።

ወለጋ ላይ ሠላም ሰፍኗል። ይህንን የሰፈነ ሰላም ማጽናት የሁሉም ትኩረት ሆኖ በአንዳንድ የኪስ በታዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን አይተናል ሲሉም ገልጸዋል።

ልማት ቀዳሚው አጀንዳ መሆኑን አይተናል፣ በከተሞቹም ሆነ በገጠር ሕዝቡ ወደ ልማት ፊቱን አዙሯል ያሉት ሚኒስትሩ ከፈተና የተማረ፣ ወደ ድል የተሻገረ እድገትና ብልጽግና መሻቱ የሆነ ቁርጠኝነትን በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥትና የአካባቢው አሥተዳደር በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በፈጠሩት ችግር የቆሙ ፕሮጀክቶች በተደራጀ መንገድ ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የተጀመረውና በፀጥታ ችግር የቆመው የቡሬ ነቀምት መንገድ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

አራቱንም የወለጋ ዞኖች ይዞ የመውጣት አቅም እንዳለው የገለጹት የነቀምት ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በከተማው ግሩም የኮርደር ልማት ሥራዎች መጀመሩን ገልጸዋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የተጀመረው የበጋ መስኖ በተለይም የስንዴ ልማት ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው እኛም በዋዩ ቱቃ ወረዳ ሚኛ ኩራ ቀበሌ በስድሳ ስድስት ሄክተር ላይ በበጋ መስኖ እየለማ ያለን የስንዴ ማሳ ተዛዋውረን ጎብኝተናል ብለዋል።

በዞኑ 228 ሺህ ሄክተር ላይ መሬት በስንዴ ዘር እንደተሸፈነ መረዳታቸውን ገልጸው የአርሶ አደሩን ምርቶች በተለይም የበቆሎ ምርት የሚያቀነባብሩ በአርሶ አደሩ ማኅበራት የለሙ የኢንዱስትሪዎችን መመልከታቸውንና ለዚህ በድጋ ወረዳ እፋ ከተማ የበቆሎ ዱቄትና ቅንጬ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በወለጋ በቆሎ በአማካይ 2 ሺህ200 ብር በኩንታል እየተሸጠ መሆኑንና ወለጋ ከግብርና አኳያ ትልቅ እምቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ለመጪው ክረምት ለአረንጓዴ ዐሻራ እየተዘጋጁ ያሉ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ላይ የቡና፣ የሙዝና አቮካዳ ችግኝ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማየታቸውን ገልጸዋል።

ወለጋ መሬቱ ከላይ ቡና ከታች ውድ ማዕድናት የሚገኙበት በሰብልም ሆነ በእንሰሳት ምርት እጅግ ትልቅ አቅም ያለው አካባቢ መሆኑን ገልጸው የተገኘውን ሰላም በማፅናት፣ የተፈጠረውን የልማት መነቃቃት በመጠናከር አካባቢውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ በጉባዔው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራን እስካሁን ከጉባዔ እስከ ጉባዔ በተገኙ ስኬቶች ላይ እየደመርን ከተጓዝን ያለምነውም እናሳካለን ሲሉም በጽሁፋቸው አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም