የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ተሰርቷል

ሐረሪ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ተሰርቷል ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ተናገሩ።
በሐረር ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ሕዝባዊ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።
በኮንፍረንሱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱልሰላም፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወየሳ ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራር አባላት ተገኝተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በቁርጠኝነት ሰርቷል።
ለአብነትም ሰፊ ቅሬታ የሚነሳበት የሕገ ወጥ መሬት ወረራና ቤት ግንባታ ችግር የክልሉ መንግስት በወሰደው እርምጃ መስተካከሉን ጠቅሰዋል።
በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህዝቡን ለምሬት የዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት መሰራቱንም እንዲሁ።
ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ከመከላከል አንፃርም ቅንጅታዊ ስራዎችን በማጠናከር ችግሩን የመፍታት ስራ ስለመከናወኑም አስረድተዋል።
ከኢንተርፕራይዞች ብድር አቅርቦት፣ ከግንባታ ፍቃድ እና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ አሰጣጥ፣ ከመሸጫ ቦታ እና ሌሎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የተደረገውን ጥረት አብራርተዋል።
መድረኩ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን አበረታች የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለማጠናከር እና ውስንነቶችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህዝብም የተለመደ ድጋፍና ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።