ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ጾም እርስ በእርስ በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፍ ይገባል -ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ

አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ጾም እርስ በእርስ በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ 1446ኛውን አመተ ሂጂራ የረመዳን ጾም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ በመግለጫቸው፥ የዘንድሮው ታላቁ የረመዳን ጾም ከሳምንት በኋላ እንደሚጀመር ገልጸው፥ ለመላው ህዝበ ሙስሊም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በጾሙ ወቅት እርስ በእርስ መዋደድ፣ይቅር መባባል እና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል።

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፥ታላቁ የረመዳን ጾም ስለ ሰላም የምንሰብክበትና አብሮነታችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በጾሙ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን አቅም በፈቀደው ልክ ለማገዝ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትም መክረዋል፡፡

በዘንድሮው የረመዳን ወር "ቁርአን የእውቀትና የሰላም ምንጭ" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የቁርአን ሒፍዝ ውድድር እንደሚካሔድና ይህም ታላቁን የረመዳን ወር ከወትሮው ለየት እንደሚያደርገው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም