በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አሶሳ፤ የካቲት 15/2017 (ኢዜአ):- በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
ሚኒስትሯ የአሶሳ ከተማን የአስፓልት መንገድ እና የኮሪደር ልማት ስራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላ ሚኒስትሯ ለሚዲያ አካላት እንደገለፁት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሰው ተኮር እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።
በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙት የአስፓልት መንገድ፣ የኮሪደር ልማት ስራ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የልማት ስራዎቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ ዜጎች የመሥራት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያደርጋል ብለዋል።
የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ስራዎች የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩና አካታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያገኘውን ሀብት በመጠቀም በከተማዋ የጀመረው የኢንቨስትመንት ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የገበያ ማዕከል እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሯ በመደመር መጽሃፍ ገቢ እየተገነባ ያለውን ሙዚየም ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።