ቀጥታ፡

ለግብርናው ዘርፍ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- ለግብርናው ዘርፍ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

በብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ኮንፍረንስ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

የውይይት መድረኩን የመሩት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)፤ በፓርቲው መሪነት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች ብዝሃ የልማት ዘርፎች የተሳኩ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በተለይም በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት።

በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ እና በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ የምርት ዕድገት ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ መሆንም አንስትዋል።

በሀገሪቱ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች የሀገርን ምጣኔ ሃብት በማሳደግና የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር በኩል ስኬታማ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የዋጋ ንረት ለመፍጠር በሚሞክሩ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፣ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር ሥራውም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የልማት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጥላሁን ቱቴ እና አቶ ያዕቆብ ቦርሳሞ፤ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች ሀገርን የሚቀይሩና ህዘብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን አንስተዋል።


 

የመንግስትን የልማት ጥረት ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት በኩል በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም