በከተማችን ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተመዘገቡ ለውጦችን እናጠናክራለን - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በከተማችን ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተመዘገቡ ለውጦችን እናጠናክራለን - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች

ዲላ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በዲላ ከተማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተመዘገቡ ለውጦችን ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በዲላ ከተማ በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የተካሄደው ህዝባዊ ኮንፍረንስ የጋራ አቋም በመያዝ ተጠናቋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማዋ በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተመዘገቡ ለውጦች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ በከተሞች መሰረታዊ ጥያቄ መሆኑን ያነሱት ተሳታፊዎቹ፣ በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ችግሩን በቅንጅት ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል መምህርት አልማዝ ዘውዴ በዲላ ከተማ በትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በአደባባይ ማስዋብና በኮሪደር ልማት ሥራዎች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተመዘገቡ ለውጦችን ከማጠናከር ባለፈ በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለመፍታት እንዲሁም በግብርናና በቱሪዝም ልማት እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት በፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ ላይ አቅጣጫ መቀመጡ የሚደገፍ ነው ብለዋል።
በዲላ ከተማ በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በዲላ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የታየው ለውጥ በአካባቢ ያለን ፀጋ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ጴጥሮስ ወቴ ናቸው።
ይሁንና በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
እንዲሁም በፌዴራልና በክልሉ መንግስታት የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በተለይ የዲላ-ቡሌ ሃሮ ዋጮ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክትና የዲላ የደረቅ ጭነት መናኸሪያ ግንባታ መፋጠን እንዳለበት አንስተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ለከተሞች እድገትና ለወጣቶች መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያነሳው ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊና ወጣት ዮሴፍ አስፋው፣ ችግሩን በቅንጅት ለመፍታት በጉባኤ አቅጣጫ መቀመጡ የሚደገፍ ነው ብሏል።
የዲላ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል ለነዋሪው የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠና ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር መሆኑን ያሳያል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዲማሜ ሌጋሞ ናቸው።
ዲላ ከተማ ከለውጡ ጋር አብራ እንድትጓዝ ለማድረግ በተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከህብረተሰቡ ለተነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ፓርቲው አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም በከተሞች የገቢ አቅምን ማሳደግ ዋነኛው መፍትሄ መሆኑ ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት አስገንዝብዋል።
በየአካባቢው የተካሄዱት ህዝባዊ ኮንፍረንሶች በከተሞች እየተመዘገበ ያለውን ልማትና እድገት ለማፋጠን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር ናቸው።
ፓርቲው በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው ጉባኤዎች ሀገርን የሚያሻግሩና የብልፅግና ጉዞን የሚያፋጥኑ አቅጣጫዎች ማስቀመጡን አንስተዋል።
በሁለተኛ የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ በኢኮኖሚ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቱሪዝም፣ በግብርናና መሰል የልማት ሥራዎች የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።