ቀጥታ፡

ባለፉት 6 ወራት ለ153 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በ2017 የመጀመርያ 6 ወራት ለ153 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ መደረጉን በኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንከ አገልግሎት የአይን ባንክ አስታወቀ።

በርካታ ዜጎች የዓይን ንቀለ ተከላ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ የዓይን ብሌን እንዲለግስም ጥሪ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንከ አገልግሎት የአይን ባንክ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አምሳለ ጌታቸው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የዓይን ባንኩ ዋና ዓላማ ሊድን በሚችል የዓይን ብሌን ጠባሳ የሚመጣ ማየት አለመቻልን ማከም ነው።

ባንኩ በሕይወት እያሉ ቃል ከገቡ ሰዎች የዓይን ብሌን በማሰባሰብ ንቅለ-ተከላውን ለሚያከናውኑ የሕክምና ተቋማት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

መሪ ስራ አስፈፃሚዋ የዓይን ብሌን ጠባሳ የሰው ልጅን ሙሉ ለሙሉ ማየት የተሳነው ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸው፤ ሕክምና ከተደረገ ሊድን እንደሚችልም አመልክተዋል።

በተያዘው በጀት አመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ለ141 ሰዎች የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ለማድረግ ታቅዶ ለ153 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የዓይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራን ቀጣይነት ባለው መልኩ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከ239 በላይ ሰዎች ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል።

ዶክተር አምሳል በዓይን ብሌን ልገሳ ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችለውን የዓይን ባንክ ማኅበር በመመስረት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት በተደረገላቸው ሕክምናና የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የዓይን ብርሃናቸው የተመለሱ ወገኖች በበጎ ፍቃድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመስራት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተለያየ ምክንያት የሚከሰተውን ዓይነስውርነት ለመከላከል የዓይን ህመም በሚያጋጥምበት ወቅት በወቅቱ ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዓይን ህመም ወይም ጉዳት በሚያጋጥምበት ወቅት ባህላዊ መድሃኒቶችን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ዶክተር አምሳለ ሰዎች ከማለፋቸው በፊት የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንዲገቡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከተመሰረተ 21 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህም ከ3 ሺህ 400 በላይ የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ-ተከላ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም