ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ተክላለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ተክላለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የቡና ምርታማነትንና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞች መትከሏን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያ 4ኛውን የጂ-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባኤን ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄም በአባል ሀገራት ተቀባይነት አግኝቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታንዛኒያ በተካሄደው 3ኛው የጂ-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
በጉባኤው ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያውያን ከቡና ጋር በባህልና በታሪክ ጭምር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው ብለዋል።
ቀደምት የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ ቡና አምራች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የቡና ምርትንና ጥራትን ለማሳደግ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት 300 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቀዋል።
ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዓለም የቡና ዋጋ መዋዠቅና የፖሊሲ ለውጦች ዘርፉን እየፈተኑት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቡና ምርታማነት አዲስ ፖሊሲ በመቅረፅ መተግበሯን ገልጸው፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የቡና ልማትን ለማረጋገጥ ደግሞ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር በማስተሳሰር እየሰራች ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዝርያቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን መትከሏን ተናግረዋል።
ይህም የቡና ስርዓተ ምህዳርን ዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ የደንና አካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርትን ለማቅረብ ወሳኝ ሚና አለው ነው ያሉት።
በቡና ኢንዱስትሪ በርካታ ወጣቶችና ሴቶች ከስራ ዕድል ፈጠራ እስከዋና የቡና አምራችነት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም አንስተዋል።
አፍሪካውያን በአጀንዳ 2063 ቡናን ስትራቴጂክ ምርት አድርገው ማካተታቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን ገልጸው፤ የቡና ዘርፍን ለማሸጋገር አህጉራዊ ኤጀንሲ መቋቋሙም ትልቅ ተነሳሽነት ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የቡና ተጠቃሚዎችን ምጣኔ ማስፋት፣ በአህጉሪቱ የቡና ንግድ ልውውጥን ማጠናከር እና የዘርፉን ኢንቨስትመንት መጨመር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ያላትን ስፍራ ለማሳደግ እንደምትሰራ ገልጸው፤ በአፍሪካ ቡናን ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
አፍሪካ ከቡና ሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን መስራት እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ ለዚህ የጋራ ራዕይ መሳካት ከሁሉም ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት 4ኛው የጂ-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባኤ በ2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ እንዲካሄድ ተወስኗል።