ቀጥታ፡

ቻይና ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት ድጋፏን እንደምታደርግ አስታወቀች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦ ቻይና ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለጀመረችው ሂደት ድጋፏን እንደምታደርግ አስታወቀች።

የንግድ ድርጅቱን በመቀላቀል ሂደት ውስጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው በዓለም የንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ አምባሳደር ቼንግጋንግ ሊ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ፀጋአብ፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ጊዜ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸው፥ ቻይና በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እና በተለያዩ መስኮች ያላት ወሳኝ ሚና አንስተዋል።

ለልዑኩ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የጀመረችውን ሂደት ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን የመቀላቀል ሂደት ውስጥ ወሳኝ ወደ ሚባለው ምዕራፍ መሸጋገሯን ገልጸዋል።

ድርጅቱን የመቀላቀል እቅዱ እውን እንዲሆን ቻይናን ጨምሮ ቁልፍ ከሆኑ የንግድ አጋር አገራት የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮች ወሳኝ እንደሆኑ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ድርድሩን ድርጅቱ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ባወጣው መመሪያ አማካኝነት ማሻሻያ በተደረገባቸው የንግድ እና አገልግሎት ምክር ሀሳቦች፣ የኢትዮጵያ የልማት ትኩረቶች እና የአባል ሀገራት ፍላጎቶችን ባከበረ መልኩ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

የሁለትዮሽ ድርድሮቹ እ.አ.አ ማርች 2025 የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ የሚመለከተው ኮሚቴ ከሚያደርገው አምስተኛው ስብስባ በፊት እንዲጠናቀቁ ጥሪ አቅርባለች።

በዓለም የንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ አምባሳደር ቼንግጋንግ ሊ ቻይና ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም የንግድ ድርጅት በምህጻረ ቃል “WTO” እ.አ.አ በ1995 የተመሰረተ ሲሆን ዋና መቀመጫው ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ነው።ድርጅቱ 166 አባል ሀገራት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም