አቶ አደም ፋራህ በቱርኩ አክ ፓርቲ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አንካራ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ አደም ፋራህ በቱርኩ አክ ፓርቲ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አንካራ ገቡ
አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የቱርኩ አክ ፓርቲ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ቱርክ አንካራ ገብተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አንካራ ሲደርሱ የአክ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አደም መሀመድን ጨምሮ የኤምባሲው አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የቱርኩ አክ ፓርቲ ከነገ ጀምሮ ጠቅላላ ጉባዔውን ያደርጋል።
ብልጽግና ፓርቲ ከፓርቲው በቀረበለት የተሳትፎ ግብዣ መሰረትም በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ አማካኝነት በመወከል በጉባዔው ላይ ተሳትፎ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ባሳለፍነው ወር በተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የቱርኩ አክ ፓርቲ በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዛፈር ሲራካያ አማካኝነት በመወከል በፓርቲው ጉባዔ ላይ ተሳትፎ አድርጓል።
ከጉባዔ ተሳትፎ በተጨማሪ ብልፅግና ፓርቲ እና አክ ፓርቲ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
በዙ መሰረት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ከስምምነቱ ፊርማ በኋላ ወደ አንካራ በመጓዝ በአክ ፓርቲ ጉባዔ ላይ ይሳተፋሉ።
ይህ መሆኑ ፓርቲዎቹ ተቀራርቦ ለመስራትና በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የጋራ አቋም የተያዘባቸው ነጥቦች ተግባራዊ እየተደረጉ የሚሄዱበትን እድል እየፈጠረ ለመሄድ እንደሚያስችል ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዘመናትን በተሻገረው የኢትዮ-ቱርክ የመንግስት ለመንግስት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር በብልፅግና እና በአክ ፓርቲ ፈር ቀዳጅነት የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ አብሮነትን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሳድገው ተገልጿል።