ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላትን ትብብር ወደ አዲስ ከፍታ የማሻገር ፍላጎት አላት-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላትን ትብብር ወደ አዲስ ከፍታ የማሻገር ፍላጎት አላት-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ እየተካሄደ የሚገኘው የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብስባ ከተጀመረ ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በስብሰባው ላይ እያደረገ ካለው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ከዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ፣ ኮመንዌልዝ እና የልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች የሀገራቱ የጋራ ጉዳይ በሆኑ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ጌዲዮን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ እና ፍሬያማ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር መዘጋጀቷን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያሏት ሰፊ እድሎች የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ፣የኢኮኖሚ እድገትን በሚያመጡ እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመስራት መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከስብስባው ጎን ለጎን ከህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር እና ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካጃ ካላስ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።