ምዕመናን የጾም ወቅትን ሰላምንና አብሮነትን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመተጋገዝ ማሳለፍ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ምዕመናን የጾም ወቅትን ሰላምንና አብሮነትን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመተጋገዝ ማሳለፍ አለባቸው
አዲስ አበባ፤የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፦ምዕመናን የጾሙን ወቅት ሰላምንና አብሮነትን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመተጋገዝ ማሳለፍ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የካቲት 17/2017 ዓ.ም የሚጀመረውን አቢይ ጾም ምክንያት በማድረግ ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ዘንድ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው አጽዋማት መካከል አቢይ ጾም አንዱ ሲሆን ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናትን፣እምነትንና ከክፉ ነገር መጠበቅን ለሰው ልጆች ያስተማረበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ምዕመኑ የጾሙን ወቅት ተምሳሌታዊ ምግባር በመከወን እንዲያሳልፍ ለማድረግም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ በጾም ወቅት ሰዎች ከምግብና ከውሃ ከመቆጠብ በዘለለ ከአንደበታቸው ለሚወጣው ቃላትና ንግግር ጭምር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፥ ከጸብና ከመነቃቀፍ መቆጠብ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በተለይም ጾሙን የተቸገሩትን በመርዳት፣የተጣሉትን በማስታረቅና ሰላምና አንድነትን የሚሰብኩ ተግባራትን በማከናወን ማሳለፍ እንደሚገባም ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መልዕክት አስተላልፈዋል።