ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አዳዲስ ስልቶች ተቀይሰው ወደ ትግበራ ተገብቷል - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አዳዲስ ስልቶች ተቀይሰው ወደ ትግበራ መገባቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።

ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን ገለጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም በኢንቨስትመንት መስክ ማነቆ ሆነው በቆዩ አሰራሮች ላይ ጥልቅ ሪፎርሞች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

በዚህም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የኢንቨስትመንት መስኮች መከፈታቸውን ጠቅሰው፤ የገቢና የወጪ ንግድ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ፍቃድን ጨምሮ ሌሎች ሪፎርሞችን ለአብነት አንስተዋል።

አሁን ላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ይበልጥ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል ሁለተኛ ምዕራፍ የሪፎርም ስራ ትግበራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ አኳያ ዓላማ ተኮር የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ዘዴን በመከተል ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑ ስመ ጥር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ከ6 መቶ በላይ ከሚሆኑ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የማግባባት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የጀመሩ ኩባንያዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጉ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ሲነሳ የነበረውን ችግር የፈታ በመሆኑ ባለሀብቶችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም በቅርቡ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መምጣቱን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

ኢትዮጵያ ባላት ዕምቅ የመልማት አቅም ከቀጣናው ሀገራት ባለፈ የአፍሪካ አህጉር ተቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል መሆኗን በማንሳት በቀጣይም ይህንኑ የማስፋት ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው ካደረጉ ሀገራት መካከል የቻይና፣ የሲንጋፖር፣ የህንድ፣ የሩሲያ፣ የጣሊያን፣ የኔዘርላንድስ፣ የጃፓን፣ የማልታ፣ የቱርኪዬ፣ የፓኪስታንና የሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች ተጠቃሽ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም