የጎንደር የልማት ስራዎች የከተማውን ታላቅነትና ታሪካዊነት የሚመጥኑ ናቸው

ጎንደር ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- በጎንደር  እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የከተማውን ታላቅነትና ታሪካዊነት የሚመጥኑ ናቸው ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩና ሌሎችም የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በከተማው በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም በሌማት ትሩፋትና በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን ጎብኝተዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)  በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤  ጎንደር በማንሰራራትና ወደ ከፍታም በመምጣት ላይ መሆኑዋን የልማት ስራዎቹ ህያው ማሳያ ናቸው፡፡


 

በኢትዮጵያ ደረጃ ቱሪዝም የእድገታችን መሰረት ነው ተብሎ ሲታሰብ እንደ አጼ ፋሲል ያሉ አብያተ መንግስታት ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አለም አቀፍ ቅርሱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የ አፍሪካ  ኩራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጎንደር ላይ የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት አፈጻጸም እየሰፋ ሲሄድ ለስራ እድል ፈጠራና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ብሎም የከተማ ነዋሪዎች የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ከተሞችን ጽዱ ፣አረንጓዴና ውብ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን ለመፍጠር በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ትልቅ ስራ እንደሆነ መመልከት ችያለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሀገር ደረጃ የእድገትና የብልጽግና ሞተር ተብለው ከተለዩ አምስት ሴክተሮች መካከል  የግብርናን፣ የኢንዱስትሪንና የኢንቨስትመንት ስራዎችን ከፍተኛ አመራሩ በከተማው ተዘዋውሮ መመልከት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የግሉ ሴክተርና  የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩና በፌዴራሉ መንግስት ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ጎንደር ከተማ እየተነቃቃች መሆኑዋን ለማረጋገጥ ችያለሁ ያሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ  እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ናቸው፡፡


 

በከተማ ግብርና እንዲሁም በስራ ፈጠራ በከተማው የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪና አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ የጎላ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት የቅርስ ጥገናና እድሳት ስራ በመደመር እሳቤ ትናንትን ዛሬንና ነገን እንዴት አስታርቀን መሄድ እንደምንችል ያየንበት ድንቅ የተግባር ውጤት ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡ 

በጉብኝቱ  የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸውን ዳኘውን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት ተሳትፈዋል፡፡

ከፍተኛ አመራር አባላቱ በጎንደር በሚካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ እንደሚካፈሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም