አቅራቢዎች መንግሥት ለዘርፉ ምርታማነት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አቅራቢዎች መንግሥት ለዘርፉ ምርታማነት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙበት ይገባል
አዲስ አበባ፤የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አቅራቢዎች መንግሥት ለዘርፉ ምርታማነት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
4ኛው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ "ጠንካራ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጥምረት ለጋራ ራዕይ ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ ሀገራዊና ቀጣናዊ ፈተናዎችን በመቋቋም ውጤታማ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አቅራቢዎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ምርትና አቅርቦት ላይ እየተሰራ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ካሉ 163 የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አቅራቢዎች መካከል የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ 20 አቅራቢዎች እውቅና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሌሎች አቅራቢዎችም ኢትዮጵያን፣አፍሪካን ብሎም ዓለምን በተዓማኒነት ያገለገሉ ድርጅቶች እንዳሉን አንዘነጋም ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የዋጋ መዋዥቅ ምክንያት የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ አቅራቢዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ህዝባችንን በማዳናቸው ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ምርትና አቅርቦት ላይ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ ነርቭ፤ ካንሰርና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የአቅራቢዎች ውስንነት እንዳለ የገለጹት ሚኒስትሯ፥ አቅራቢዎች መንግሥት የፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የአገራችንን ብሎም የአህጉራችንን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር እና ሌሎች ቀጣናዊ የጤና ተቋማትን በመጠቀም ኢትዮጵያን ለሌሎች አገራት ምሳሌ ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፥ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች በማምረት ለውጥ ማምጣቷን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ አቅራቢዎች ጉባኤ ውድ መድሀኒቶችን በቀላሉ ማስገባትና የሀገር ውስጥ ምርትን በዓይነትና በጥራት ማሻሻል ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ጓንት፣የህክምና መርፌ ማምረት እንዲሁም የአልትራሳውንድ መሳሪያ በአገር ውስጥ መገጣጠም የሚያስችል ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው፥ መንግስት የወሰዳቸው የፖሊሲ እርምጃዎች የጤናውን ዘርፍ ምርታማነት በእጅጉ ማሻሻሉን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሙሉ በሙሉ በመፍታት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ሽፋን ከሪፎርሙ በፊት ከነበረበት ስምንት በመቶ ወደ 36 በመቶ ማሳደግ አስችሏል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት ከአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል እና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የገዛቸውን ስድስት ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ግምት ያላቸው 62 የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን ማጓጓዣ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ለክልሎች አስረክቧል፡፡