ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል -የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡-የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እና አረንጓዴ ልማት ጉዳዮች ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በአስር አመቱ መሪ የልማት እቅድ ጨምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን እውን ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች።  

በተለያዩ የዘርፍ ተቋማት የልማት እቅድና ፕሮግራሞች ውስጥ ለማስረጽ የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የፓሪስ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድን በመቅረፅ እ.አ.አ እስከ 2050 የምትመራባቸው እቅዶችና ስትራቴጂዎች መቅረጿን ገልጸዋል። 

በዚህም በአገሪቱ እስከ 2030 የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ68 ነጥብ 8 በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አመርቂ እንዳልነበር የገለጹት ዶክተር ፍፁም፤ ይህም አስፈላጊው ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ እንደነበር  አንስተዋል።

አሁን ላይ ሚኒስቴሩ የግሉን ዘርፍ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚያስተባብር የስራ ክፍል ማደራጀቱንም ጠቁመዋል።  

ከባለድርሻ አካላት ጋር ትብብርን በማጠናከርና በአየር ንብረት ፋይናንስ ማፈላለግ ላይ በማተኮር የአገሪቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  


 

የአለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንኤል ኦቦናያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት በመቀነስ በኩል በርካታ ስራዎችን በማከናወን አበረታች ውጤቶች ማስመዝገቧን ተናግረዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ለሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ልማት እና ትግበራ የመንግስት፣ ግሉ ዘርፍና አለም አቀፍ ተቋማት ጠንካራ ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት። 

ኢንስቲትዩቱም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንና ይህንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 


 

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም መንግስት በዘረጋቸው አሰራሮች ዙሪያ የግሉ ዘርፍ ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 

በዚህም ለኢኮኖሚ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖን ለመቋቋም እየተደረገ ላለው ተግባር የፋይናንስ አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ለማሳካት የአየር ንብረት የፋይናንስ ምንጮችን በማግኘት በኩልም የግሉ ዘርፍ የበኩሉን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።

ለአርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂ የሚያቀርበው መኮቡ ኢንተርፕራይዝ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰብለ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የተለያዩ የሶላር ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርበው የአብራ አምባ ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ተድላ በበኩላቸው አውደጥናቱ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከሚኒስቴሩ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም