ህጻናት የተሟላ ህክምና የሚያገኙበትን ምቹ የጤና ተቋማትን የመገንባት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ህጻናት የተሟላ ህክምና የሚያገኙበትን ምቹ የጤና ተቋማትን የመገንባት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦ህጻናት የተሟላ ህክምና የሚያገኙበትን ምቹ የጤና ተቋማትን የመገንባት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጿል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የህፃናት አንጎልና ህብለ ሰረሰር የቀዶ ህክምና የልህቀት ማዕከል በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተገንብቶ ተመርቋል።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መዲናችን በአፍሪካ ደረጃ ህጻናትን በአግባቡ በማሳደግ ምቹ እና ተመራጭ እንድትሆን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ልጆችን ለማሳደግ ምቹ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ጤናቸው በአግባቡ እንዲጠበቅ የሚያስችሉ የህክምና ተቋማትን ማስፋፋት አለብን ብለዋል።
የቀዶ ህክምና የልህቀት ማዕከሉ ስራ መጀመር በህጻናት ጤና እንክብካቤ ላይ የሚሰሩ ተግባራት አመርቂ ውጤት እንዲኖራቸው አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ህጻናት የጤና እክል ሲገጥማቸው ህክምና የሚያገኙበት ምቹ የጤና ተቋም እንዲኖር ከተማ አስተዳደሩ የሚሰራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የህክምና ተቋማትን ለማሻሻል የሚጠበቅበትን ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የማዕከሉ መከፈት እንደ ሀገር ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለማዕከሉ ግንባታ እገዛ ያደረገው የሪች አናዘር ፋወንዴሽን በጤናው ዘርፍ ላይ ለሚከናወኑ ስራዎች ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የህፃናት አንጎልና ህብለ ሰረሰር የቀዶ ህክምና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችና የተሟላ የህክምና መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ግብአቶችን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሳደግና የህክምና ባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የልህቀት ማዕከሉ በመዲናዋ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
ማዕከሉም ለህጻናት ተገቢውን ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ግብአቶች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ 64 አልጋዎች፣ሁለት ዘመናዊ የኦፕሬሽን ክፍሎች ፣128 ስላይስ ሲቲ ስካን እና ሰርጂካል ማይክሮ ስኮችን ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን መያዙን አስረድተዋል።
የሪች አናዘር ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ፓትሪሽያ ኦኔል በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ የህጻናትን ጤና ለመጠበቅ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ማዕከሉ የህጻናትን ጤና ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶች የሚጎለብቱበት መሆኑንም አክለዋል።
የማዕከሉ የግንባታ ወጪ በሪች አናዘር ፋውንዴሽን እንደተሸፈነ ተገልጿል።