የኢትዮጵያ እና ህንድ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ መጠን እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ህንድ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ መጠን እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ እና ህንድ ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ምጣኔ እያደገ መምጣቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስሚን ወሃብረቢ፥ ከህንድ የንግድ ልዑካን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ኢትዮጵያ እና ህንድ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ የዲፕሎማሲ ትብብር እንዳላቸው እና የንግድ ትስስራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የህንድ የኢትዮጵያ የቅባት እህሎች ኤክስፖርት መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፏን ለውጪ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ እና የንግድና የቁጥጥር ስርዓቷን በማዘመን እያከናወነች ያለው ስራ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዳደረጋት አመልክተዋል።
የህንድ ንግድ ልዑካን ቡድን አባላት በበኩላቸው በኢትዮጵያ በንግድ አቅም ግንባታ፣በሎጂስቲክስ እና በሌሎችም ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ልዑካኑ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ግቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከልን መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።