ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ጽኑ ፍላጎት አላት-ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የሁለትዮሽ ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ እየተካሄደ የሚገኘው የቡድን 20 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብስባ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፥ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ሚኒስትሩ ከስብስባው ጎን ለጎን የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች እና የደህነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ካጃ ካላስ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ባለው የሁለትዮሽ ትስስር እንዲሁም የጋራ ጉዳዮቻቸው በሆኑ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ተለዋውጠዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነች መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።