ቀጥታ፡

የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ

ጅግጅጋ ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) ክትባትን እንደሚከተቡ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።


 

ሀገር አቀፉ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በይፋ ተካሂዷል።

በክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሃይማኖትና አባቶች ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ የፖሊዮ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚከናወነውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ህብረተሰቡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ሊያስከትብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ በበኩላቸው የፖሊዮ በሽታን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በመደበኛም ሆነ በዘመቻ ሰፋፊ የክትባት አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ከአጎራባች ሀገራት ጋር የቅንጅት ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ የቅኝት ስራዎችም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው በክልሉ የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በተከናወነው ስራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

ለውጤቱም በማህበረሰቡ ላይ ይስተዋል የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት መቅረፍ በመቻሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ እንደገለፁት ከዛሬ ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በዘጠኝ ክልሎች ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ይካሄዳል።

ከዛሬ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በሚሰጠው በዚሁ የክትባት ዘመቻም 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ህፃናት እንደሚከተቡ ገልፀዋል።

ክትባቱ ከቤት ለቤት አገልግሎት በተጨማሪ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህፃናት ማቆያና በጤና ተቋማትና በሌሎች በነፃ እንደሚሰጠጥም ጠቁመዋል።

ለዚህም ከ84ሺህ በላይ ባለሙያዎች ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በቀጣይም በሽታውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም