በክልሉ ታህታይ አዲያቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ታህታይ አዲያቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው
ሽረ እንዳስላሴ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ታህታይ አዲያቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
በዞኑ አሰተዳደር የስነ አዝርዕት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ አባይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዞኑ በታህታይ አዲያቦ ወረዳ በአንድ ሺህ 226 ሄክታር ደን ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በነቃ የህዝብ ተሳትፎ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።
ባለፋት ሁለት ቀናት በኬሚካል ርጭትና በሰው ኃይል በተደረገው የተቀናጀ የመከላከል ሥራ 175 ሄክታር ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ መከላከል መቻሉን ገልፀዋል።
በደን እና በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሰውን የአንበጣ መንጋ ካረፈበት ቦታ ሳይቀሳቀስ ለመከላከል አንድ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የተናገሩት ባለሙያው ወደ አጎራባች ወረዳዎች እንዳይዛመትም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአንበጣ መንጋውን ጥቃት በአጭር ጊዜ ለመግታት የነዳጅ እጥረት እክል እየፈጠረ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ችግሩን ለማቃለል ድጋፍ መስጠት እንዳለበትም ተጠይቋል።