ቀጥታ፡

ኢንዱስትሪዎች በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ ሚናቸው እንዲጎላ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ ሆነዋል - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በእጥፍ በማሳደግ በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕደገት ላይ ሚናቸው እንዲጎላ የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

ሶስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።

ኤክስፖውን አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ለአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ተወካዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ የማድረስ ግብ ይዛ እየሰራች ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪዎች ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት መንግስት የህግና የአሰራር ስርዓትን ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎች ማድረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።

የተመዘገበው ውጤት በ10 ዓመቱ የልማት ግብ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ ለማድረስ የተያዘው ግብ እውን መሆን እንደሚችል ማሳያ ነው ብለዋል።

መንግስት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በእጥፍ በማሳደግ በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ ሚናቸው እንዲጎላ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ ያጋጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑንም አስታውቀዋል።


 

ውድድርን የሚገቱ ህጎችና አሰራሮችን ለመቀየር በየደረጃው ያለው አመራር ያሳየው ቁርጠኝነት በዘርፉ እየታየ ላለው ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄደው የኢትዮጰያ ታምርት ኤክስፖ ሙሉ ወጪ በአምራች ኢንዱስትሪዎቹ መሸፈኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ መንግስት ዘርፉን ለመደገፍ ካለው ፍላጎት አኳያ የ3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ግማሽ ወጪ ይሸፍናል ብለዋል።

በኤክስፖው ላይ ከ265 በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡና ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በተጨማሪም ከሀገር ውስጥና ከውጭ በርካታ የንግድ ስምምነቶችና የገበያ ትስስሮች እንደሚፈጠሩበትም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም