በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባትሪ ሃይል መሙላት የሚያችሉ ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባትሪ ሃይል መሙላት የሚያችሉ ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባትሪ ሃይል መሙላት የሚያችሉ ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው ሜጋ አንፊ ቲያትር ያስገነባው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ መሙያ ጣቢያ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደገለጹት በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ሃይል መሙላት የሚያችሉ ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከተማ አስተዳደሩ ያስገነባው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ሃይል መሙያ ጣቢያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የንግድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ መሙያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጣቢያው በአንድ ጊዜ 16 ተሽከርካሪዎችን ሃይል መሙላት እንደሚያስችል ገልፀው እንደመኪኖቹ አይነት ሙሉ ቻርጅ ለማድረግ እስከ 40 ደቂቃ እንደሚወስድም ጠቁመዋል።
የከባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ታዳሽ ሀይልን ከማስፋትና የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አንፃር አስተዋፅኦ ያላቸውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚነት ለማስፋት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ጣቢያው በውስጡ 1ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችል ሲኒማቲክ ስክሪን የተገጠመለት አንፊ ቲያትር፣ 2 የህዝብ መዝናኛ ካፍቴሪያዎች እና የህጻናት ማቆያ እንዳሉትም ገልጸዋል።
እንዲሁም 800 ኪሎ ዋት ዝግጁ ጄኔሬተር ያለው ሲሆን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የተደገፈ የሴኪዩሪቲ ሲስተም እንደተገጠመለትም ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተበራከቱ መምጣት ጋር ተያይዞ ከመንግስት ባሻገር የግል ባለሃብቱም አዋጪነቱን በመመልከት ወደ ዘርፉ እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።