በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው - ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳሬክተር ይታሰብ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት አና ፍላጎትን ለማመጣጠን በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦና ፍላጎት ያለበትን ደረጃ ለመለየት ሀገራዊ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ አገልግሎት የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማቅረብ አኳያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግል ኮሌጆች፣ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሎጆች ያሉበትን ደረጃ መፈተሹን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት አኳያ ያሉትን ክፍተቶች ብሎም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት አቅርቦትና ፍላጎት ምን ይመስላል የሚለውን መፈተሹን ገልጸዋል።
የተገኙ ውጤቶችም በቱሪስት ደረጃ ባሉ ሆቴሎች እና ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ያሉ ሆቴሎች ላይ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል 47 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አሰራር ዘርፉን የሚያቀጭጭና ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የቱሪስት ፍላጎት መዳረሻዎችን የሚመጥን አለመሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በቀጣይ አምስት ዓመታት ይህን ክፍተት ለመሙላትና በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሚፈለገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የራዛፕ አስጎብኚ ድርጅት ተወካይ አፍራ መሐመድ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ከመስፋፋታቸው ጋር ተያይዞ የቱሪስት ፍሰቱ መጨመሩን ተናግረዋል።
ለዚህም መንግስትና በዘርፉ ያሉ አካላትን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማስጎብኘት ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ ለማግኘት ቋንቋ ላይ አሁንም ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም የቱሪዝም ዘርፉን የበለጠ ለማዘመንና አገልግሎቱን ለማስፋት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች ማንዋሎች ሊዘጋጁ እንደሚገባ ተናግረዋል።