በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል- ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል- ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓትን በመገንባት ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ጠየቁ።
በአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ የግሉን ዘርፍ ፋይናንስ ነክ ተሳትፎን ለማጠናከር ያለመ ዐውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ተቀበላ እየተገበረች ነው ብለዋል።
በመሪ የልማት ዕቅዷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው በመጠቆም።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓትን በመገንባት ሂደት የግሉ ዘርፍ በንቃትና በመሪነት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
ለአብነትም በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም በሚያስፈልጉ የፋይናንስ አቅርቦት ረገድ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ጋር አጋርነት ማጠናከር እንደሚሻ ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንኤል ኦቦናያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር)፥ የግሉ ዘርፍ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።