ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ ምርቶችን ማምረትና አቅርቦቱን ማሳለጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ ምርቶችን ማምረትና አቅርቦቱን ማሳለጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጹ።

4ኛው ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ "ለጋራ ርዕይ ጠንካራ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፋዊ ጥምረት መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎን ጨምሮ የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ፣ ዓለም አቀፍ የመድሃኒት አቅራቢዎች ተወካዮች እና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ቀጣይነት ያለው እና ቀልጣፋ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው።

ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎችን በማምረት ለውጥ አምጥታለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያ ምርቶችን ማምረትና አቅርቦቱን ማሳለጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

በሶስተኛው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ጉባኤ ብዙ ነገሮችን በማሻሻል ተጨባጭ ግቦችን ማሳካት ችለናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ጓንት፣ የህክምና መርፌ ማምረት ጀምረናል ያሉት ዶክተር አብዱልቃድር፣ የአልትራሳውንድ መሳሪያ በሀገር ውስጥ በመገጣጠም እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ለመድኃኒት ምርት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ለህክምና ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያ ማድረጉ ለዘርፉ እድገት የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል።

በመሆኑም እንደ ሀገር ያሉ መልካም እድሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያዎች ማምረቻ ማዕከል ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም