ቀጥታ፡

በክልሉ በፀሐይ ኃይል አማራጭ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ነው

ጋምቤላ፤ የካቲት 14/2017 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ከዋና መስመር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎችን በፀሐይ ኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በአገልግሎቱ የጋምቤላ ክልል ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ብርሃኑ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የፀሐይ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ ነው።


 

በተለይም ከኤሌክትሪክ የኃይል መስመር የራቁ ከተሞችና ቀበሌዎች በጸሀይ ኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ይደረጋሉ ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ233 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አንድ የወረዳ ከተማና በአምስት የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከነዚህም መካከል አራቱ የፀሐይ የኃይል አማራጮች ናቸው ብለዋል።

በ27 የትምህርትና የጤና ተቋማት በፀሐሀይ ኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

የአገለግሎቱ ፕሮጀክቶች ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር እንዳለ በላቸው እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ በዚህ ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት ይበቃል።

በክልሉ 83 ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች በመስመርና በፀሐይ ኃይል አማራጭ ተጠቃሚ እንደሆኑ የአገልግሎቱ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም