ቀጥታ፡

ሉሲዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከዩጋንዳ ጋር ያካሂዳል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት 30 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሀምዝ ስታዲየም ይከናወናል።

በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ካምፓላ መግባቱ ይታወቃል።

ቡድኑ ለሁለት ቀናት ልምምዱን በሀምዝ ስታዲየም አድርጓል። የመጨረሻ ልምምዱንም ጨዋታው በሚደረግበት ስታዲየም ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ዩጋንዳን ካሸነፉ በሁለተኛው ዙር ከታንዛንያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ መርሃ ግብሩ በሁለት ዙር እንደሚከናወን እና 38 ሀገራት እየተሳተፉ እንደሚገኙ  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

11 ሀገራት ከአዘጋጇ ሞሮኮ ውጪ በአህጉራዊው መድረክ ለመሳተፍ ይፋለማሉ።

በአፍሪካ ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም