ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።

በቤልጂዬም፣ በኔዘርላንድስ፣ በሉክሰምበርግና በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኔዘርላንድስ ንጉስ ዊሌን አሌክሳንደር አቅርበዋል።

በዚሁ ጊዜም አምባሳደሩ እሸቴ ከንጉስ አሌክሳንደር ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር እሸቴ በቆይታቸው ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ በንግድ፣ በአንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ትስስር መጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋለ።

ንጉስ አሌክሳንደር በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ረጂም ዘመን የዘለቀ ታሪካዊ ወዳጀነትና ትብብር እንዳላቸው ገልጸው፤ ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ከሆኑት ከጄልቴ ቫን ዋይረን ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ምህዳር ለማስፋት እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነትን አብራርተዋል።

ጄልቴ ቫን ዋይረን በበኩለቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ያላትን ቁልፍ ሚና አድንቀዋል።

ኔዘርላንድስ ኢትዮጵያ ቁልፍ ተዋናይ በሆነችበት የአፍሪካ ቀንድ ትብብሯን ማጠናከር እንደምትሻም ጠቁመዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።


 

በተመሳሳይ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብቶች መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ማርክ ዘለንራት ጋር በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

አምባሳደር እሸቴ በሁለቱ ሀገራት መካከል በፍልሰት፣ በጸጥታና በልማት ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ትብብር መጥቀሳቸውን ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ማርክ ዘለንራት የኢትዮ-ኔዘርላንድ የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን መሻት ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም