ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች በአዲስ አበባ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤የካቲት 13 /2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮች፣ ሠራተኞች እና የአየር መንገዱ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እና ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።

ጉብኝቱ  የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ ማዕከል እና ሌሎችንም የልማት ስራዎችን ያካተተ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት እያከናወናቸው ካሉ የምገባ ማዕከላትና መሰል ፕሮጀክቶችም የጉብኝቱ አካል ነበሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዋና መዲና ተብላ የምትጠራው አዲስ አበባ ያሏት የተለያዩ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ስፍራዎች ከተለያዩ ሀገራት በሚያጓጉዛቸው መንገደኞች እንዲጎበኙ ለማድረግ እንደሚሠራም አስታውቋል ።

በተለይም “ኢቲ ሆሊደይስ” በሚባለውና ቱሪዝም ላይ አተኩሮ በሚሰራው የስራ ክፍሉ አማካይነት በአዲስ አበባ በቂ የቆይታ ግዜ ላላቸው ትራንዚት መንገደኞች የከተማ ጉብኝት ጥቅል (Stop Over Package) በማዘጋጀት የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት ከፍ ለማድረግ ብሔራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል እንደሚገኝ ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
#Ethiopian_News_Agency  #Ethiopia  #ኢዜአ
#የኢትዮጵያአየርመንገድ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም