በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ጤና ነክ መረጃዎች ትክክለኛና ተዓማኒ መሆን አለባቸው- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ጤና ነክ መረጃዎች ትክክለኛና ተዓማኒ መሆን አለባቸው- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፦ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ጤና ነክ መረጃዎች ተዓማኒነታቸውና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጡ እንዲሆኑ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ተገቢ ያልሆኑ መረጃ የሚለቁ የጤና ባለሙያዎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በጤና ተቋማት፣ በጤና ባለሙያዎች እና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዙሪያ የሚዲያ፣ የፍትህ እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፥ የጤና መረጃዎች በቅጡ ካልተላለፉ ዘርፉንም የማህበረሰቡን ጤና አጠባበቅ ስርዐት ለአደጋ የሚዳርጉ ናቸው።
መገናኛ ብዙሃን ጤና ነክ መረጃዎችና ማስታወቂያዎች ከማስተላለፋቸው በፊት ተአማኒነትና ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ፈቃድ ስላላቸው ብቻ ተገቢ ያልሆኑ የጤና መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እያሰራጩ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ ድርጊት መቆጠብ ይገባል ብለዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሳይንሳዊ ሂደት ባልተከተለ መልኩ የማይድኑ በሽታዎችን ጭምር እናድናለን የሚሉ ግለሰቦችእንዳሉ ገልፀው፤ ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ ውዥንብርን በመፍጠር የጤና ስርዓቱ ላይ ስጋት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ ጤና ነክ መረጃና ማስታወቂያን ከማሰራጨት እንዲቀጠቡ አሳስበዋል።
የፍትህ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላትም የጤና ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ እንዳይሰራጭ የመከላከልና የመቆጣጠር ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በጤና ሚኒስቴር የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ እንዳልካቸው ጸዳል በበኩላቸው፥ ትክክለኛነት የጎደለው የተጋነነ ማስታወቂያ ህብረተሰቡን እየፈተነ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አፋጣኝ ምላሽን የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው የጤና ሚኒስቴር እንደተቆጣጣሪ አካል በባለሙያዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የፍትህ ተቋማት መሰል ድርጊቶች እንዲታረሙ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማስታወቂያ ክትትል ዴስክ ሃላፊ በድሪያ ውልጫፎ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የህክምና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ጥንቃቄ የተሞላባቸው መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አሳሳች የሆኑ አገላለጾች፣ የማይሰጡ አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እንዲሁም ሀሰተኛ ምስክርነትን የሚጠቀሙ ማስታወቂያዎች አየር ላይ መዋል እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በውይይቱ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ስራዎቻቸውን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚያከናውኑ አረጋግጠዋል።