ተሽከርካሪዎች አስገዳጅ የ3ኛ ወገን መድን እንዲገቡ በማድረግ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር ይገባል

አዳማ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- ተሽከርካሪዎች አስገዳጅ የ3ኛ ወገን መድን እንዲገቡ በማድረግ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስገነዘበ።

አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ 3ኛ ወገን መድን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች የሚደርስ የትራፊ አደጋ የሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሀመድ ሀሰን እንዳስታወቁት አገልግሎቱ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን የሞት፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ እየሰራ ነው።

በተለይ በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ለሚደርስባቸው ተጎጂዎች ካሣ በመክፈል፣ የአስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት የሕይወትና የአካል ጉዳት ካሳ ክፍያ በመፈጸም የአደጋ ተጎጂዎች የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶች ለመቀነስ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል።

ለካሳ ክፍያ ከሚውለው ገንዘብ በአግባቡ እየተመለሰ አለመሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ቅንጅት መጠናከር አለበት ብለዋል።


 

አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙና የመንግስት ወጪንም ለማስመለስ አገልግሎቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘርፉ አዲስ የወጡ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ መስራት እንዲቻል መድረኩ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከሁለቱ ከተማ አስተዳድሮችና ከክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም